ቲክቶዶክስ
በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
19፥34 ይህ የመርየም ልጅ ዒሣ ነው፡፡ ያ “በ”እርሱ የሚከራከሩበት እውነተኛ ቃል ነው፡፡ ذَٰلِكَ عِيسَى ٱبْنُ مَرْيَمَ ۚ قَوْلَ ٱلْحَقِّ ٱلَّذِى فِيهِ يَمْتَرُونَ
የመሬቷ ኦርቶዶክስ የጽብሓውያን ኦርቶዶክስ"Oriental Orthodox" ሲሆን ቲክ ቶክ ላይ ያለው ኦርቶዶክስ ደግሞ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ"Eastern Orthodox" ነው፥ ቲክ ቶክ ላይ ያለው ኦርቶዶክስ የሽሙጥ እና የለበጣ ስሙ "ቲክቶዶክስ" ሲሆን በጽብሓውያን ኦርቶዶክስ ማሊያ ለምሥራቅ ኦርቶዶክስ የሚጫወት ነው። ይህ ስውር አጀንዳ የምሥራቅ ኦርቶዶክስን ትምህርት በቅጡ እና በአግባብ ያልተረዳ ሰው አያውቀውም፥ ቲክቶዶክስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ትውፊትን፣ አዋልድን፣ ሃይማኖተ አበውን እና ሊቃውንትን ጭምር ሳይቀር የማይቀበልበት እና የሚንቅበት ምክንያት ለዛ ነው።
"ፊሲስ" φύσις ማለት "ባሕርይ" ማለት ሲሆን "ምንነት" ነው፥ "ሒፓስታቲስ" ὑπόστασις ማለት "አካል" ማለት ሲሆን "ማንነት" ማለት ነው።
፨ "ክርስቶስ ከማርያም የሰው ባሕርይ"Human Nature" እንጂ የሰው አካል"human Hypostasis" አልነሳም" የሚሉ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ በላቲን "አን ሒፓስታሲያ"An Hypostasia" ሲባሉ "አን ሒፓስታቲስ" ἀν ὑπόστασις ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ነው። "አን ሒፓስታቲስ" ἀν ὑπόστασις ማለት "ኢ አካል" ማለት ነው፥ አን" ἀν ማለት አፍራሽ ሲሆን ኢ"Not" ማለት ነው። "ኢየሱስ የመለኮት አካል እንጂ የሰው አካል የለውም" የሚለው የቲክቶዶክስ ትምህርት ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ የተቀዳ ነው፥ ይህንን ለማረጋገጥ ለቲክቶዶክስ "ኢየሱስ የሰው አካል አለው ወይስ የለውም" ብሎ መጠየቅ ብቻ በቂ ነው።
፨ "ክርስቶስ ከማርያም የሰው ባሕርይ"human nature" ብቻ ሳይሆን የሰው አካል"human Hypostasis" ነስቷል" የሚሉ የጽብሓውያን ኦርቶዶክስ በላቲን "ኤን ሒፓስታሲያ"En Hypostasia" ሲባሉ "ኤን ሒፓስታቲስ" ἐν ὑπόστασις ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ነው። "ኤን ሒፓስታቲስ" ἐν ὑπόστασις ማለት "በ አካል" ማለት ነው፥ ኤን" ἐν ማለት አውንታዊ ሲሆን በ"In" ማለት ነው። ይህ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አቋም ነው፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 73 ቁጥር 3
"እርሱ ወልድ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆነ"።
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 94 ቁጥር 13
"ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ከሁለት አካል አንድ አካል እንደሆነ እርሱን እናውቃለን"።
ሁለት ባሕርይ የአምላክ ባሕርይ እና የሰው ባሕርይ ሲሆኑ "ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ" ማለት "የአምላክ ባሕርይ እና የሰው ባሕርይ አንድ ሆነ" ማለታቸው ነው፥ እንዲሁ ሁለት አካል የአምላክ አካል እና የሰው አካል ሲሆኑ "ከሁለት አካል አንድ አካል" ማለት "የአምላክ አካል እና የሰው አካል አንድ ሆነ" ማለታቸው ነው።
ከዚህ በተቃራኒው ቲክ ቶክ ላይ ያሉ የቲክቶኩ ኦርቶዶክስ "ወልድ የአምላክነት አካል እንጂ የሰውነት አካል የለውም" የሚለው ትምህርት የቃረሙት፣ የገበዩት እና የቀሰሙት ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ ነው፥ የሚያሳዝነው ቲክቶዶክስ በጉባኤ ቤት ወይም መጽሐፍ ቤት ሊገቡ ይቅርና ንባብ ቤት ገብተው ስለማያውቁ ግዕዝ እንኳን ለማንበብ አይሞክሩም።
በኢሥላም ነገረ ክርስቶስ ኢየሱስ ምንነቱ የሰው ምንነት ሲሆን ማንነቱ የሰው ማንነት ነው፥ በምንነቱ የማርያም ልጅ ሲሆን በማንነቱ ነቢይ፣ መልእክተኛ እና መሢሕ ነው። እንግዲህ አምላካችን አሏህ ስለ ዒሣ ምንነት እና ማንነት በቁርኣን የነገረን ቃል እውነተኛ ቃል ነው፦
19፥34 ይህ የመርየም ልጅ ዒሣ ነው፡፡ ያ “በ”እርሱ የሚከራከሩበት እውነተኛ ቃል ነው፡፡ ذَٰلِكَ عِيسَى ٱبْنُ مَرْيَمَ ۚ قَوْلَ ٱلْحَقِّ ٱلَّذِى فِيهِ يَمْتَرُونَ
“የምተሩነ” يَمْتَرُونَ ማለት “የሚከራከሩበት” ማለት ሲሆን በታሪክ ውስጥ ብዙ ሰዎች በዒሣ ምንነት እና ማንነት ቢከራከሩበትም አሏህ ስለ ዒሣ የነገረን ግን እውነተኛ ንግግር ነው፥ “ሂ” هِ ማለትም “እርሱ” የተባለው ዒሣ ሲሆን “እርሱ” በሚለው መነሻ ቅጥያ ላይ “ፊ” فِي የሚል መስተዋድድ ሲኖር “ስለ”About” በሚል የመጣ ነው። አምላካችን አሏህ በትንሣኤ ቀን በዚያ በእርሱ ትለያዩበት በነበራችሁት ሁሉ በመካከላችሁ ይፈርዳል፦
22፥69 አሏህ በትንሣኤ ቀን በዚያ በእርሱ ትለያዩበት በነበራችሁት ሁሉ በመካከላችሁ ይፈርዳል፡፡ اللَّهُ يَحْكُمُ بَيْنَكُمْ يَوْمَ الْقِيَامَةِ فِيمَا كُنتُمْ فِيهِ تَخْتَلِفُونَ
አምላካችን አሏህ በዒሣ ዙሪያ የምትወዛገቡትን ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።
✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም